ኢትዮ-ፎረምና ዛራ ሚዲያን የመሳሰሉ ከTigray People’s Liberation Front (ቲ.ፒ.ኤል.ኤፍ), ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ህልዉና ጋር ቁርኝት ያላቸዉ ሚዲያዎች በንቃት ወደ ጸረ-ኦሮሞ ህዝብ እንቅስቃሴ መድረክነት መገልበጣቸዉና የተዛቡና ሃሰተኛ የፍብረካ መረጃዎችን በኦሮሞ ህዝብና ትግል ላይ በስፋት ማሰራጨታቸዉ በጣም ያሳዝናል፡፡ ይህ ዘመቻቸዉ በተለይ የገነገነዉም በቅርቡ ኦ.ነ.ግ እና ኦ.ፌ.ኮ ከብዙሃኑ የኦሮሞ ህዝቦቻቸዉ ተወካዮች ጋር የተመካከሩበትን መድረክ ተከትሎ ነዉ፡፡ በእርግጥ ጤነኛ አእምሮና ሚዛናዊ ህሊና ላለዉ ሰዉ በዘመናት የጦርነት አዙሪት ሳቢያ የህዝቡ ህይወት ወደ ገሃነምነት የተቀየረበት ህዝብ ለሠላም የሚያደርገዉ መፍጨርጨር ያስደስተዋል ተብሎ ይገመታል፡፡ ይሁን እንጂ የዘሬ ያንዘርዝረኝ እንዲሉ፤ ድሪቶዉ የሃበሻ አሻጥር ሁለቱን የትግራዋይ ትላልቅ ሚዲያዎች ወደ ማዕበሉ ስቦ በማስገባት ጦርነትና ጭቆና ዘማሪ አድርጓቸዋል፡፡ የዉስጠ – ትግራይ የፖለቲካ ትኩሳት አደጋ አሳሳቢ ሆኖ እያለ፤ ዳግም ኦሮሚያን የመግዛትና ሃብቷን የመበዝበዝ ድብቅ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ህልም ገፍቶ በመዉጣት ወቅታዊ የቲ.ፒ.ኤል. ኤፍ የፖለቲካ አጀንዳ ሆኖ ወጥቷል፡፡
የሁለቱ ሚዲያዎችና የሌሎችም ጋሻ ጃግሬዎቻቸዉ የመረጃ ምንጮች ያልተረጋገጡ የማህበራዊ ድረ-ገጾች አሉባልታዎች፤ ከስም አልባ የመንግሥት አካላት አገኘን የሚሏቸዉ ወሬዎች፤ ወዘተ ናቸዉ፡፡ ሪፖርቶቻቸዉም የኦሮሞን የፖለቲካ ድርጅቶችና ብሎም የኦሮሞን ህዝብ ለማናናቅ፤ ለማጣጣል፤ ለማሸማቀቅ፤ ተስፋ ለማስቆረጥ ታቅደዉ የሚሠሩ ናቸዉ፡፡ በትግራይ ዉስጥና በኦሮሚያም ዉስጥ ላሉት አስከፊ ግጭቶች ዘላቂ ሠላም ለማምጣት ከፖለቲካ ድርጅቶቹ ጋር ተባብረዉ ከመሥራት ይልቅ ከኦሮሞ ህዝብና ድርጅቶች ጋር ሆን ብለዉ ጠብን፤ ጥላቻን፤ ግጭትን ማራገብ መርጠዉ ቀጥለዋል፡፡
ሰሞኑን የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፤ ህዝባዊ ማህበራት፤ የሃይማኖት ተቋማት፤ ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦች ተሰብስበዉ ስለህዝባቸዉ ሠላምና ህልዉና፤ስለ ህዝቡ መጻኢ እድል … ወዘተ በመመካከራቸዉ ብቻ ሚዲያዎቹ ስብሰባዉ በብልጽግና ፓርቲ የተደራጀና የአቢይ፤ የኦ.ነ.ግ እና የኦ.ፌ.ኮ የመድረክ ላይ የቀልድ ድራማ አስመስለዉ ዘግበዋል፡፡ በስብሰባዉም ላይ ሽመልስና አዳነች ታዳሚ እንደሚሆኑና ስብሰባዉ በአቢይ እንደሚዘጋም ተርከዋል፡፡ የዚህን ታሪካዊና ጠቃሚ ስብሰባ ዘገባ በዝርዝርና በግልጽ ማየት እንደሚቻለዉ (ይህን በመንካት) አንድም የብልጽግና ፓርቲ አባል ሽመልስና አዳነችንም ጨምሮ አልተሳተፉበትም፡፡ የስብሰባዉ ተሳታፊዎች ከ100 ስለማይበልጡ ኢትዮ-ፎረምና ዛራ ሚዲያ እዉነቱን ማወቅ ቢፈልጉ ኖሮ ተሰብሳቢዎቹን በሙሉ ማየት ስለሚችሉ ሀቁ ዳገት አይሆንባቸዉም ነበር፡፡ ዳሩ ግን የኢትዮ-ፎረም ዓላማ የኦሮሞን የነጻነት ትግል ጥላሸት መቀባት እንጂ እዉነቱን መዘገብ አይደለም፡፡ ለዚህም ነዉ የሃሰት ዘገባዉን (ይህን በመንካት ያገኙታል) ዛሬም ድረስ ያላረመዉ፤ ወይም ያላስተባበለዉ፡፡
የሚያስገርመዉ፤ እነዚህ ዛሬ ይህንን የሚዘግቡት ምንጮች፤ ቲ.ፒ.ኤል.ኤፍ በኦሮሞ ህዝብ ላይ ለ27 ዓመታት ምድራዊ ሲዖል የሆነ ግፍ ሲፈጽም ለታሪክ አንድም ቃል ያልተነፈሱ ጉዶች መሆናቸዉ ነዉ፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ገበሬዎች፤ መምህራን፤ ተማሪዎች፤ነጋዴዎች የኦ.ነ.ግነት ታርጋ እየተለጠፈባቸዉ እስር ቤቶችን አጨናንቀዉ፤ እስር ቤቶች የኦሮሞ ቋንቋ ተናጋሪዎች ማደርያ መሆናቸዉን የቀድሞዉ የቲ.ፒ.ኤል. ኤፍ መሪ አቶ ስዬ አብርሃ ጭምር በመሰከሩበት ጊዜ እንኳ ኢትዮ-ፎረምና ዛራ ሚዲያ ስለ እዉነታዉ ምንም አልዘገቡም፡፡
ሚዲያዎቹ በቲ.ፒ.ኤል. ኤፍ ጥያቄ ከሱዳን ስደተኞች ጣቢያ በሃይል ተገድደዉ ወደ ኦሮሚያ እንዲመለሱ ተደርገዉ በቲ.ፒ.ኤል. ኤፍ ስለ ተገደሉትና፤ ተገድደዉ ስለ ተደፈሩት ሺዎች ኦሮሞዎች ምንም አልተነፈሱም፡፡
ስለእሬቻዉ የኦሮሞ ጅምላ ጭፍጨፋ፤ ስለ ምሥራቅ ኦሮሚያዉ የወተር ጅምላ ጭፍጨፋ፤ ከኦሮሚያዉ ሠላማዊ ተቃዉሞ በቲ.ፒ.ኤል. ኤፍ አግአዚ ጦር እየተመዘዙ በኦሮሚያ ጎዳናዎች ላይ ስለታነቁት 7000 ኦሮሞ ወጣቶች አልተናገሩም (ሪፖርቱን ይህን በመንካት ያገኙታል)፡፡
በቲ.ፒ.ኤል. ኤፍ ተይዘዉ መዉደቅያቸዉ ሳይታወቅ ስለቀሩት ሺዎች ምሁራን፤ መምህራን፤የፖለቲካ መሪዎች አንዳችም አልተነፈሱም፡፡ ባህልንና ማንነትን ለማጥፋት ስለተደረጉ ግፎች፤ ስለፈረሱት የኦሮሞ የባህል ተቋማት፤ስለ ደበሱ ጉዮ ግድያ ምንም አልተቹም፡፡
ሁለቱ ሚዲያዎች ከቄዬአቸዉ፤ ከይዞታቸዉ፤ ከንብረታቸዉ፤ ከአገራቸዉ ተገድደዉ ስለተፈናቀሉትና መሬታቸዉ ለቲ.ፒ.ኤል. ኤፍ ጄነራሎችና ካድሬዎች ለተቀራመተዉ ሚሊዮኖቹ የኦሮሞ ገበሬዎች የዘገቡት ነገር የለም፡፡ ሚዲያዎቹ ለኦሮሞ መሬት ወረራ ታቅዶ ስለቀረበዉና ለሺዎች ኦሮሞዎች እስራት፤ ስደትና ሞት ምክንያት ስለሆነዉ የቲ.ፒ.ኤል. ኤፍ የፊንፊኔ ማስተር ፕላን ክለሳ ያቀረቡት ተቃዉሞ የለም፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮ-ፎረምና ዛራ ሚዲያ የተመሠረቱት የቲ.ፒ.ኤል. ኤፍን የፖለቲካ ካምፕ ዓላማና ግብ ለማስጠበቅ እንጂ እዉነትን ለማገልገል፤ በእዉነት ላይ ለመመሥረት፤እዉነት ላይ ለማተኮር አይደለም፡፡ ትግራዋይ ያልሆነ ተበዳይ አይታያቸዉም፡፡ የጋዜጠኝነት የሙያ ሥነ ምግባር ይጎድላቸዋል፡፡ ቲ.ፒ.ኤል. ኤፍ የሚያደርሰዉን ግፍና በደል መስማት አይሹም፡፡ በቲ.ፒ.ኤል. ኤፍ እና በመሪያቸዉ መለስ ዜናዊ የተፈጸሙትን ዘር ማጥፋቶችና በደሎች ጋርደዉና ሸፋፍነዉ ለመኳል ይፈጋሉ፡፡ የትግራይ ክልል በጦርነት ተጽእኖዎች፤ በሙስና፤ በመጥፎ አገዛዝ፤ በረሃብና በዉስጣዊ የፖለቲካ መከፋፈል ተወጥሮ ባለበት በዚህ ከባድ ወቅት እንኳ ሁለቱ ሚዲያዎች ከቲ.ፒ.ኤል. ኤፍ ደህንነትና ስለላ ዋና ሃላፊ ከጌታቸዉ አሰፋ የተጫነባቸዉን የፖለቲካ የበላይነት አሮጌ ድብዳብ ተጣብቀዉ መቀጠላቸዉ ይገርማል፡፡ እዚህ ላይ ቲ.ፒ.ኤል. ኤፍ ኦሮሞዎች ላይ ያደረሳቸዉን ወንጀሎች በምሳሌነት ጠቀስን እንጂ ኦሮሞ ያልሆኑ የቲ.ፒ.ኤል. ኤፍ ተጠቂዎች የሉም ለማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ይህን ይጫኑ::
ሁለቱ ሚዲያዎች ለፈጠራቸዉ ቲ.ፒ.ኤል. ኤፍ ታማኞች ሆነዉ ያገለግላሉ፡፡ ቲ.ፒ.ኤል. ኤፍ በስልጣን ላይ በቆየባቸዉ ከ1991 እስከ 2018 ድረስ በነበሩት ጊዜያት ለተጨፈጨፉት ሺዎች ኦሮሞዎች ግንባር ቀደም ተጠያቂዉ የቲ.ፒ.ኤል. ኤፍ ደህንነት ሃላፊና ዋና ሰላዩ ጌታቸዉ አሰፋ ነዉ፡፡ የአሁኑ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንትና የቲ.ፒ.ኤል. ኤፍ ማእከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ጌታቸዉ ረዳ ከርዕዮት ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ በመለስ ዜናዊ አመራር ሥር ከባድ ጥፋቶችና ጉድለቶች ቢኖሩም መለስን ዝነኛ ለማድረግና ችግሮቹን ለመሸፋፈን ለእነዚህ ሚዲያዎች ቲ.ፒ.ኤል. ኤፍ ገንዘብ ይከፍላቸዉ እንደነበር አረጋግጠዋል፡፡
ለትግራይ ህዝብ ጥቅም ሲባል ቲ.ፒ.ኤል. ኤፍ እና ሁለቱ ሚዲያዎች ከስህተታቸዉ መታረም፤ ትክክለኛዉን መዘገብ፤ ሚዛናዊ ሆነዉ የፖለቲካ ቀማኛዎቹን ሳይሆን የትግራይን ህዝብ ማገልገል ይጠበቅባቸዋል፡፡ በሠላም ጥረቶች ላይ ጸረ – ፕሮፓጋንዳ ማድረግ አይጠበቅባቸዉም፡፡ ቲ.ፒ.ኤል. ኤፍ እንደ ኦ.ፒ.ዲ.ኦ ዓይነት ዲቃላ ድርጅትን በ2025 በኦሮሚያ ለመመስረት ለሚያደርገዉ ሙከራ ባያወግዙትም መራቅ አለባቸዉ፡፡ ከዚህ በኋላ የትግራይ ሠላም የሚወሰነዉ ከነጻ የኦሮሞ ድርጅቶች ጋር በመተባበር እንጂ ዲቃላ የኦሮሞ ድርጅቶችን በመፍጠር አይደለም፡፡ ሁለቱ ሚዲያዎችና ቲ.ፒ.ኤል. ኤፍ አሮጌና መርዛማ የሆነዉን የተንኮል ሽረባ ድሪቶ የሚያራግፉበት ጊዜ አሁን ነዉ፡፡ የተንኮል ሽረባዉ በድጋሚ ይሠራል ብሎ ማሰብ እብደት ነዉ፡፡ የቲ.ፒ.ኤል. ኤፍ ማገገሚያ ቅርጽ ይሄዉ ነዉ፡፡ ነገር ግን ሚዲያዎቹ እና አንዳንድ በአሮጌ የሥልጣን ማማ ላይ ተንጠልጥለዉ የቀሩ ህልመኛ አመራሮች ዛሬ ላይ ሆነዉ የ1990 ዉን ህልም ይቃዣሉ፡፡ ከ2020 እስከ 2022 ድረስ መጠነ ሰፊ ጥፋት ካስከተለዉ ጦርነት በፊት የያዙትን ሠይፍ ዛሬም ያወዛዉዛሉ፤ሊያስፈራሬበትም ይዳዳቸዋል፡፡
ለማጠቃለል፤ በቅድሚያ የታሪክ ጠጣር እዉነት መታመን አለበት፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ይቅር ሊል ይችላል፡፡ ነገር ግን በቲ.ፒ.ኤል. ኤፍ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ. መንግሥት ሥር ያሳለፋቸዉን ምስቅልቅሎች ፈጽሞ አይረሳቸዉም፡፡ የቲ.ፒ.ኤል. ኤፍ ጠባሳዎችና አሻራዎች ለኦሮሞዎች ትኩስና ህያዉ ናቸዉ፡፡ በመለስ ዜናዊ አገዛዝ ሥር የተፈጸሙ ግፎችን ለማስታወስ የተቀነጠሱ ክንዶች፤ የፈረሱ ትዳሮች፤ አሳዳጊ ያጡ ጨቅላዎች፤ የተቃወሱ ህሊናዎች፤የተፈናቀሉ ቤተሰቦች ተጨባጭ ህይወቶች የየዕለቱ ኮርኳሪ ደወሎች ናቸዉ፡፡ ቲ.ፒ.ኤል. ኤፍ እና የሚዲያ ምንጮቹ የመለስንና እህአዴግን ዘመናት ወንጀሎች ቅዱስ የማድረግ ጥረታቸዉን ሊያቆሙ ይገባል፡፡ በኦሮሞ የዉስጥ ጉዳዮች ጣትን መስደድ ጥርጣሬንና አለመተማመንን መፍጠር ብሎም የህዝቡን ችግር ከማራዘም ዉጪ ሌላ ፋይዳ ሊኖረዉ አይችልም፡፡ የኦሮሞ ህዝብ የፍትህ እና የነጻነት ጥማት እና ትግል በተለያዩ አካላት አሻጥራዊ ስልት፤ በመከፋፈል፤ በደባና ሽረባ ሊኮላሽ፤ ሊሸበሸብና ሊቆም እንደማይችል ካለፉት 35 የቲ.ፒ.ኤል. ኤፍ የተማከለ የፖለቲካ አገዛዝ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ወደ ተሟላ ነጻነት የሚያደርገዉን ጉዞ ቲ.ፒ.ኤል. ኤፍ ወይም ማንም የፖለቲካ ሃይል ፈጽሞ ሊያስቆመዉ አይችልም፡፡ ይህንን ሃቅ በጸጋ መቀበል ለቲ.ፒ.ኤል. ኤፍም ሆነ ለመላዉ የኦሮሞ ህዝብ እጅግ ጠቃሚ ነዉ፡፡
ዳንኤል ፊዶ





















